ቴስላ ሳይበርትራክ ተሽከርካሪ ምርትን እንደሚያቆም ገለፀ!
የቴስላ ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኤሎን መስክ፤ ኩባንያቸው በሚቀጥለው ዓመት በቴክሳስ በሚገኘው ፋብሪካው የሚያካሂደውን የሳይበርትራክ ተሽከርካሪዎች ምርት በከፍተኛ ደረጃ እንደሚቀንስ አስታውቀዋል።
ኤሎን መስክ ተሽከርካሪዎቹን ሙሉ በሙሉ የማምረት ሒደቱ እንደሚቆም ወይም የምርት ቦታው ወደ ሌላ ስፍራ እንደሚዛወር በግልጽ አላብራሩም። ሆኖም ውሳኔው ሙሉ በሙሉ በራሳቸው ለሚንቀሳቀሱት አዲሶቹ «ሳይበርካብ» (Cybercab) መኪኖች የማምረቻ ስፍራ ሰፊ ዕድል ለመስጠት ታስቦ የተወሰነ መሆኑን ገልጸዋል።
በሌላ በኩል የፕሮጀክቱ ዋና መሐንዲስ ዌስ ሞሪል ተሽከርካሪው ሙሉ በሙሉ ከገበያ ሊወጣ እንደሚችል ፍንጭ ሰጥተዋል። መሐንዲሱ «ኤክስ» በተሰኘው የማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት፦ "ሳይበርትራክ እጅግ አስደናቂ የቴክኖሎጂ ልማት መድረክ የነበረ ሲሆን፤ አሁን ደግሞ በሳይበርካብ አማካኝነት ህያው ሆኖ ይቀጥላል" ብለዋል።
ልዩ በሆነው ባለሦስት ማዕዘን ቅርፅና ውጫዊ ገጽታው በርካታ አድናቂዎችን ስቦ የነበረው ሳይበርትራክ፤ እ.ኤ.አ. በ2023 ለገበያ ከመቅረቡ በፊት በተደጋጋሚ በምርት መዘግየት ችግሮች ሲፈተን የቆየ ሲሆን፤ ለገበያ ከቀረበ በኋላም ያስመዘገበው የሽያጭ መጠን ዝቅተኛና ተስፋ አስቆራጭ መሆኑ ተነግሯል ።
#afromekina
Loading content...
