ታክሲ ከመንቀሳቀሱ በፊት ክፍያ እንዲከፈል የሚያስገድድ መመሪያ ተዘጋጀ
የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ የታክሲ አሽከርካሪዎች ከተወሰነው ታሪፍ በላይ በማስከፈል በህዝቡ ላይ የሚፈጥሩትን ቅሬታ ለመቅረፍ፤ ጉዞ ከመጀመሩ በፊት ክፍያ የሚያስገድድ አዲስ አሠራር መዘርጋቱን አስታውቋል።
የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ዳኛቸው ሽፈራው እንደገለጹት፣ አሽከርካሪዎች በታሪፉ መሠረት ብቻ ከመነሻው እንዲያስከፍሉ ለማድረግ ተቆጣጣሪዎች በመጫኛ ቦታዎች ላይ ተመድበው ሥራ ጀምረዋል። ይህ አሠራር በመንገድ ላይ “ሒሳብ ጨምሩ” የሚሉ አግባብነት የሌላቸውን ጭቅጭቆችና ብዝበዛዎች ለመግታት ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል ተብሎ ታምኖበታል።
ሆኖም አዲሱ አሠራር ተግባራዊ መደረጉን ተከትሎ፣ በመነሻዎች ላይ ክፍያ አስቀድሞ ለመሰብሰብ የሚፈጀው ጊዜ መራዘም በማኅበረሰቡ ዘንድ ቅሬታ መፍጠሩ ተገልጿል። በተጨማሪም አንዳንድ አሽከርካሪዎች አሁንም መንገድ ላይ ታሪፍ የመጨመር አዝማሚያ እያሳዩ በመሆኑ፣ ማኅበረሰቡ ሕገ-ወጦችን በመጠቆም እንዲተባበር ጥሪ ቀርቧል። ቢሮው በአሁኑ ወቅት ትኩረቱን በዚህ አዲስ አሠራር ላይ ማድረጉን ጠቁሞ፣ ከዚህ ቀደም አከራካሪ በነበረው የረዳት (ወያላ) አጠቃቀም ላይም ወደፊት ግልጽና ወጥ የሆነ የአሠራር ሥርዓት እንደሚዘረጋ አስታውቋል።
#afromekina
Loading content...
