የነዳጅ ቦቴ ባለንብረቶች ከገበያ ልንወጣ እንችላለን ሲሉ ስጋታቸውን ገለጹ
በሀገሪቱ እየታየ ያለው የመለዋወጫ እቃዎች ዋጋ መናር እና የታሪፍ ማሻሻያ አለመደረግ አክሳሪ እንደሆነባቸው የገለጹት የፈሳሽ ጭነት ማጓጓዣ ባለንብረቶች፣ ችግሩ ባልተፈታበት ሁኔታ ስራቸውን ማስቀጠል አስቸጋሪ እንደሆነባቸው በመግለጽ ከገበያው የመወጣት ስጋት እንደደቀነባቸው አስታወቁ።
የኢትዮጵያ የፈሳሽ ጭነት ማጓጓዣ ባለንብረቶች ማህበር የነዳጅ ፍላጎት እድገትን እና የወጡ ወጪዎችን ያገናዘበ የታሪፍ ማሻሻያ እንዲደረግ ተደጋጋሚ ጥናቶችን ማቅረቡን ያስታወሰ ቢሆንም፣ በመንግስት በኩል ግን እስካሁን አዎንታዊ ምላሽ ማግኘት አለመቻሉን ገልጿል።
የማህበሩ ፕሬዝደንት አቶ ፀጋ አስማረ እንደገለጹት፤ ጥናቱ ዝም ብሎ የቀረበ ሳይሆን ከነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን፣ ከትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር እንዲሁም ከንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከተወጣጡ ባለሙያዎች ጋር በጥጋቢ ሁኔታ ተጠናቆ የቀረበ ነው። ሆኖም ምላሽ በመዘግየቱ አባላቱ ለአላስፈላጊ ክሳራ መዳረጋቸውን አብራርተዋል።
ከታሪፍ መዘገየት በተጨማሪ ባለንብረቶች ሌላ አጣብቂኝ ውስጥ የከተታቸው አሽከርካሪዎች ከባለንብረቱ እውቅና ውጪ በሚፈጽሙት የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ ምክንያት ተሽከርካሪዎች እና ነዳጅ የመወረስ እርምጃ እየተወሰደባቸው ይገኛል ብለዋል።
ይህንን ተከትሎ የኢትዮጵያ የፈሳሽ ጭነት ትራንስፖርት ባለንብረቶች ማህበር አባላቱን በመጥራት በዘርፉ በተደቀኑ ዘርፈ-ብዙ ችግሮች እና በቀጣይ የጋራ አቋሞች ዙሪያ የምክክር ስብሰባ አካሂዷል።
#afromekina
Loading content...
