የበካይ ጋዝ ልቀታቸው ከፍተኛ የሆኑ ተሽከርካሪዎችን በካሜራ እየለየን እያገድን መሄዳችን የማይቀር ነው" - አቶ አስመሮም ብርሃኔ
በተያዘው የበጀት ዓመት 200 ተሽከርካሪዎች (111 ቤንዚን እና 89 ናፍጣ) ላይ በተደረገ ምርመራ የወጣውን የበካይ ጋዝ ልቀት ደረጃ ያሟሉት 55.5 በመቶ ያህሉ ብቻ መሆናቸውን የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ገልጿል።
ከቤንዚን ተሽከርካሪዎች መካከል 101ዱ፥ 91 በመቶ ውጤት አስመዝግበው መስፈርቱን ማሟላት መቻላቸውን ገልጸዋል። በአንጻሩ፥ ከ89 የናፍጣ ተሽከርካሪዎች ውስጥ መስፈርቱን ማሟላት የቻሉት 13 ብቻ መሆናቸው ነው የተነገረው።
ቢሮው በጉዳዩ ላይ ከሰሞኑ ባከናወነው የውይይት መድረክ ላይ የተገኙት የትራንስፖርት መሠረተ ልማት ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ አስመሮም ብርሃኔ፥ "የችግሩን አሳሳቢነት ሁሉም መረዳት አለበት፣ ህግን የማያከብሩ ተሽከርካሪዎች ላይ እስከ ማገድ የሚደርስ እርምጃ እንወስዳለን" ሲሉ ተናግረዋል።
አቶ አስመሮም አክለውም፥ "መመሪያው ከወጣ በኋላ የተሰጠው የችሮታ ጊዜ አሁን ላይ አብቅቷል" ያሉ ሲሆን እስካሁን የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ሲሰራ መቆየቱን አንስተዋል።
እስካሁንም "በካይ ነህ" ተብሎ ከከተማ እንዲወጣ የተደረገ አንድም ተሽከርካሪ አለመኖሩን በማስታወስ "ለአዲስ አበባ የማይመጥኑ ተሽከርካሪዎች አሉ፣ በሂደት ግን ከተማዋን የሚመጥኑ መሆን አለባቸው" ሲሉ አክለዋል።
"እንደዚህ ሆነን አንቀጥልም፣ በሚቀጥሉት ጊዜያት ወደ እርምጃ ወደ መውሰድ እንመጣለን። የበካይ ጋዝ ልቀታቸው ከፍተኛ የሆኑ ተሽከርካሪዎችን በካሜራ እየለየን እያገድን መሄዳችን የማይቀር ነው" ሲሉ ነው ምክትል የቢሮ ኃላፊው የተናገሩት።
እርምጃው የሚወሰደው የከተማዋን የትራንስፖርት አቅርቦት በማይጎዳ እንዲሁም አሮጌ ተሽከርካሪዎች የብዙ ቤተሰቦች የገቢ ምንጭ በመሆናቸው በአንድ ጊዜ ከሥራ ውጪ ማድረግ የሰዎችን ጉሮሮ መዝጋት ስለሚሆን ቀስ በቀስ እንዲተኩ በሚደረግ መሆኑን ኃላፊው በመድረኩ አክለው ገልጸዋል።
አቶ አስመሮም ብርሃኔ፥ "ባለ አሮጌ አሽከርካሪዎች አዲስ ተሽከርካሪ ገዝተው መተካት እንዲችሉ መንግስት የብድር አቅርቦት ማመቻቸት አለበት" ሲሉ አንስተው "ለዚህም 85፤ 90 በመቶው በብድር ሆኖ እየሰሩ የሚከፍሉበትን መንገድ የማመቻቸት ስራ እየሰራን ነው" ብለዋል።
ከመጠን በላይ በካይ ጭስ የሚያወጡ ተሽከርካሪዎች የብክለት መቀነሻ ቴክኖሎጂ እንዲጠቀሙም አሳስበዋል።
#afromekina
Loading content...
