በአዲስ አበባ የመኪና ንግድ ማዕከላት ላይ ሰፊ የግብር ስወራ መኖሩ ተጋለጠ።
የአዲስ አበባ ከተማ ገቢዎች ቢሮ በከተማዋ በሚገኙ የመኪና ንግድ ማዕከላትና የመኪና ድለላ ዘርፍ ላይ ባካሄደው ምርመራ ሰፊ የሆነ የግብር ስወራ መኖሩን እንደደረሰበት ካፒታል ጋዜጣ ዘግቧል።
በመኪና ንግድና ደላላ ሥራ የተሰማሩ አካላት ዓመታዊ የገቢ ግብርና የተጨማሪ እሴት ታክስ (VAT) ግዴታቸውን በአግባቡ እንደማይወጡ የቢሮው ጥናት አሳይቷል።
ይህን ተከትሎም በመኪና ደላላነት / በኮሚሽን ንግድ የሚሰሩ ነጋዴዎች በግቢያቸው ያስቀመጧቸውን መኪኖች እንዲያስወጡ ጥብቅ ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸው ነበር።
ቢሮው እንደገለጸው፣ መኪናዎችን ለሽያጭ በማይፈቀድላቸው ቦታዎች ማስቀመጥና መሸጥ ከሕጋዊ የንግድ ደንቦች ጋር የሚጋጭ ነው።
ቢሮው ባወጣው መመሪያ፣ በሕጋዊ መንገድ የተመዘገቡ የመኪና አስመጪ ድርጅቶች ብቻ በተፈቀደላቸው የንግድ ቦታ መኪና መሸጥ እንደሚችሉ በግልጽ አስቀምጧል።
ከሰሞኑን በአዲስ አበባ በትክክል አስመጪ ያልሆኑና በኮሚሽን የሚሰሩ እጅግ በርካታ የመኪና መሸጫዎች ተዘግተው ነበር።
አሁን ላይ በተሻሻለ መመሪያ ሥራቸውን እንዲቀጥሉ ተፈቅዶላቸዋል። ሆኖም የመኪና ነጋዴዎች የሚሰሩበት ሥርዓት ላይ ገደቦች ተጥለዋል።
በተለይም አዲስና ያልተነዱ "Zero-Mile" መኪኖችን በግል ኮሚሽን ወይም ትርፍ ላይ ተመስርቶ መሸጥ እንዲሁም እነዚህን መኪኖች በራሳቸው ግቢ ውስጥ መሸጥ አይፈቀድም።
አዲስ መኪኖችን የማስመጣትና የመሸጥ መብት ሕጋዊ ፈቃድ ላላቸው አስመጪዎች ብቻ ተሰጥቷል።
በሌላ በኩል፥ የመኪና ደላላዎች በግለሰቦች የተያዙ ያገለገሉ መኪኖችን በኮሚሽን መሸጥ ወይም መኪና በራሳቸው ገዝተው እንደገና መሸጥ ይችላሉ፤ ይህም ግን የተቀመጡትን የግብርና የንግድ ሕጎች በመከተል ብቻ መሆን አለበት።
#afromekina
Loading content...
