ዳንጎቴ ሊገነባ ላሰበው ትልቁ የነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካ ኬንያን መረጠ
ኩባንያው በ17 ቢሊዮን ዶላር ወጪ በቀን 700 ሺህ በርሜል ነዳጅ የሚያጣሪያ ፋብሪካ ነው።
አፍሪካዊው ቢሊየነር አሊኮ ዳንጎቴ በ17 ቢሊዮን ዶላር ወጪ በቀን 700 ሺህ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ የማጣራት አቅም ያለው ፋብሪካ ለመገንባት ኬንያን መምረጣቸውን ተዘገበ። የምሥራቅ አፍሪካ ግዙፉ የነዳጅ ማጣሪያ ተቋም ይሆናል የተባለው ይህ ፕሮጀክት፥ ቀጠናው ከውጭ በሚገቡ የነዳጅ ምርቶች ላይ ያለውን ጥገኝነት እንደሚቀንስ እና የኃይል ዋስትናን እንደሚያጠናክር ይጠበቃል።
የነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካው በኬንያ የህንድ ውቅያኖስ ጠረፍ ላይ በምትገኘው ላሙ ላይ የሚገነባ ሲሆን፥ የግንባታው ቦታ ምርጫ ተጠናቆ የአፈር ምርመራን፣ ምሕንድስናን እና ዲዛይንን ጨምሮ የመጀመሪያ ደረጃ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
ግንባታው ሦስት ዓመታት ገደማ ሊፈጅ እንደሚችል እና ፋብሪካው ለኬንያ እንዲሁም ለጎረቤት ሀገራት ዩጋንዳ፣ ታንዛኒያ እና ደቡብ ሱዳን የነዳጅ ምርቶችን እንደሚያቀርብ ተዘግቧል።
ይህ የነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካ በናይጄሪያ ከሚገኘው የዳንጎቴ ዋና ማጣሪያ ፋብሪካ ጋር ተመጣጣኝ የማጣራት አቅም የሚኖረው ሲሆን፥ ይህም ኩባንያው የነዳጅ ማጣራት አቅሙን በመላው አፍሪካ ለማስፋፋት የያዘው ሰፊ ስትራቴጂ አካል ነው ተብሏል።
በተጨማሪም ይህ ኢንቨስትመንት እጅግ ከፍተኛ የሆነ የሥራ ዕድል የሚፈጥር እና በቀጠናው ያለውን የኢንዱስትሪ ዕድገት የሚደግፍ ነው። የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ ለፕሮጀክቱ ድጋፋቸውን የገለጹ ሲሆን፥ አፈጻጸሙን የሚከታተል የመንግሥት አስተባባሪ ኮሚቴ አቋቁመዋል።
#afromekina
Loading content...
