ከአውሮፕላን ጋር የሚፎካከረው አዲሱ የቻይና ፈጣን ባቡር!
በቻይና ሁቤይ የሚገኘው የዶንግሁ ላቦራቶሪ በአንድ ኪሎ ሜትር የሙከራ መንገድ ላይ አዲስ የቴክኖሎጂ ስኬት አስመዝግቧል። 1,110 ኪሎ ግራም የሚመዝነው የቻይና የኤሌክትሮማግኔቲክ ባቡር፣ በ5.3 ሰከንድ ውስጥ ብቻ ከቆመበት ተነስቶ በሰዓት 800 ኪሎ ሜትር ፍጥነት መጋለብ ችሏል።
ይህ ፍጥነት ከአንዳንድ የመንገደኞች አውሮፕላን የበረራ ፍጥነት ጋር የሚስተካከል ሲሆን፣ ባቡሩ በአጭር ርቀት ውስጥ በደህና መቆም እንደሚችልም አሳይቷል። የሲሲቲቪ ዘገባ እንደገለፀው፣ ባቡሩ በስድስት ወራት ውስጥ የራሱን የፍጥነት ሪከርድ ሲያሻሽል ይህ ለሦስተኛ ጊዜ ነው።
ነገር ግን ተጓዦች በቅርብ ጊዜ ውስጥ በዚህ ባቡር ይሳፈራሉ ተብሎ አይጠበቅም። ባቡሩ ባለው ከፍተኛ ፍጥነትና ኃይለኛ ስበት ምክንያት፣ ቴክኖሎጂው ለወደፊቱ ይበልጥ ጥቅም ላይ የሚውለው ለጠፈር ሮኬቶች፣ ለድሮኖችና ለወታደራዊ አውሮፕላኖች መነሻነት ነው። ይህም አውሮፕላኖችና ሮኬቶች ከመሬት ሲነሱ የሚጨርሱትን ከፍተኛ የነዳጅ መጠን ለመቀነስ ይረዳል።
በአሁኑ ወቅት ሰዎችን የሚያጓጉዙት የቻይና ፈጣን ባቡሮች በሰዓት 350 ኪሎ ሜትር የሚጓዙ ሲሆን፣ አዲሱ የሙከራ ባቡር ግን ለወደፊቱ የትራንስፖርትና የጠፈር ምርምር ትልቅ በር የከፈተ አዲስ ፈጠራ ሆኗል።
#afromekina
Loading content...
