በአፍሪካ ትልቁ ኩባንያ ወደ ኢትዮጵያ
ገበያ ለመግባት እየተዘጋጀ ነው
በአፍሪካ ትልቁ የኤሌክትሪክ ትራንስፖርት ኩባንያ የሆነው ስፒሮ፣ የባትሪ መለዋወጫ መረቡን ለማስፋፋትና ወደ አዳዲስ ገበያዎች ለመግባት የሚያስችለውን የ215 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት ማግኘቱን አስታወቀ። በዴንማርክ ኢምፓክት ፈንድ እና በኤኩዊቴን የተደገፈው ይህ የገንዘብ ማሰባሰብ፣ ኩባንያው ወደ ኢትዮጵያና ወደ ኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ እንዲገባ ትልቅ አቅም ይፈጥርለታል።
በአሁኑ ወቅት ስፒሮ በሰባት የአፍሪካ ሀገራት (ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ኡጋንዳ፣ ቶጎ፣ ቤኒን፣ ናይጄሪያ እና ካሜሩን) ውስጥ ከ100,000 በላይ የኤሌክትሪክ ሞተር ብስክሌቶችን ያሰማራ ሲሆን፣ ከ2,500 በላይ የስማርት ባትሪ መለዋወጫ ጣቢያዎችን በመገንባት እስካሁን ከ30 ሚሊዮን በላይ የባትሪ ቅያሬዎችን አከናውኗል። በተጨማሪም ኩባንያው በኬንያ፣ ሩዋንዳና ኡጋንዳ የማምረቻ ፋብሪካዎች ያሉት ሲሆን፣ በናይጄሪያ ደግሞ የባትሪ መልሶ ጥቅም ላይ ማዋያ (recycling) ማዕከል በመክፈት ከ6,000 በላይ ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆኑ የስራ እድሎችን መፍጠር ችሏል።
ይህ አዲስ ኢንቨስትመንት የስፒሮን የቴክኖሎጂ እድገትና የመገጣጠም አቅም ከማሳደጉም በላይ፣ ለሞተር አሽከርካሪዎች የዕለት ተዕለት የትራንስፖርት ወጪን እስከ 40 በመቶ በመቀነስ በቀን እስከ 2 ዶላር የሚደርስ ቁጠባ ያስገኝላቸዋል። ስፒሮ ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት ማቀዱ፣ ሀገሪቱ ከጥር 2016 ዓ.ም ጀምሮ በነዳጅ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባትን ማገዷንና ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የቀረጥ እፎይታ መስጠቷን ተከትሎ የመጣ ትልቅ ዕድል ነው።
Loading content...
