በዓለም ገበያ የነዳጅ ዋጋ ቀነሰ
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቬንዙዌላ ከ30 እስከ 50 ሚሊዮን በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ለአሜሪካ እንደምታቀርብ ማስታወቃቸውን ተከትሎ፣ የዓለም የነዳጅ ዋጋ ከአንድ በመቶ በላይ መቀነሱን ዘ ጋርዲያን ረቡዕ ዕለት ዘግቧል።
ዓለም አቀፍ መለኪያ የሆነው የብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ ረቡዕ ዕለት ከአንድ በርሜል ከ60 ዶላር በታች የወረደ ሲሆን፣ የአሜሪካ ድፍድፍ ነዳጅ ደግሞ በ1.4 በመቶ ቀንሶ 56.44 ዶላር ሆኗል።
የአሜሪካው ጣልቃ ገብነት ቬንዙዌላ ወደ ቻይና የምታደርገው የነዳጅ ኤክስፖርት ሊያቋርጥ ይችላል የሚል ስጋትንም ፈጥሯል።
ይህች የላቲን አሜሪካ ሀገር ከምታመርተው ድፍድፍ ነዳጅ ውስጥ 80 በመቶ የሚሆነውን ወደ ቻይና ትልካለች። ይህም ቤጂንግ ለድፍድፍ ነዳጅ ከፍተኛ ዋጋ እንድትከፍል ሊያስገድዳትና ከዋይት ሀውስ ጋር ያለውን ውጥረት ሊያባብሰው ይችላል።
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ረቡዕ ዕለት በሰጠው መግለጫ ቬንዙዌላ "በተፈጥሮ ሀብቷና በኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎቿ ላይ ሙሉ እና ቋሚ ሉዓላዊነት አላት" ብሏል።
አክሎም አሜሪካ ነዳጁ ለሷ እንዲሰጥ ያቀረበችው ጥያቄ "ዓለም አቀፍ ሕግን የሚጥስ፣ የቬንዙዌላን ሉዓላዊነት የሚጋፋ እና የቬንዙዌላን ሕዝብ መብት የሚጎዳ ነው" ሲል ገልጿል።
ቀደም ብሎ ትራምፕ "ትሩዝ ሶሻል" በተሰኘው የማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፦ "እንደ አሜሪካ ፕሬዝዳንትነቴ ይህ ገንዘብ ለቬንዙዌላ እና ለአሜሪካ ሕዝቦች ጥቅም እንዲውል እቆጣጠረዋለሁ... ይህ ነዳጅ በመርከብ ተጭኖ በቀጥታ በአሜሪካ ወደሚገኙ የመጫኛ ወደቦች ይመጣል" ብለው ነበር።
#afromekina
Loading content...
