በኢትዮጵያ በአማካኝ ከአንድ ቦቴ 500 ሊትር ነዳጅ ይቀሸባል ተባለ
አገሪቷን በዓመት 5.5 ቢሊየን ብር የሚያከስረው የነዳጅ ዘረፋ በቴክኖሎጂ ሊገታ ነው
በኢትዮጵያ የነዳጅ ስርጭት ሂደት ውስጥ ለዓመታት ስር ሰዶ የቆየውንና ለአገር ኢኮኖሚ ትልቅ ጠንቅ የሆነውን የነዳጅ ስርቆትና ቅሸባ ለመግታት፣ መንግስት አዲስ የቴክኖሎጂ ሥርዓት ተግባራዊ ሊያደርግ መሆኑን አስታውቋል።
የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን እንዳጠናቀቀው ጥናት ከሆነ፣ በየዓመቱ ከ5.5 ቢሊየን ብር በላይ የሚገመት ነዳጅ በማጓጓዝ ሂደት ላይ በህገ-ወጥ መንገድ ይቀሸባል።
የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ደስታው መኳንንት ለአሐዱ እንደገለጹት፣ በአሁኑ ወቅት በአማካይ ከአንድ የነዳጅ ጫኝ ተሽከርካሪ (ቦቴ) ላይ ብቻ እስከ 500 ሊትር ነዳጅ በህገ-ወጥ መንገድ ይቀሸባል።
ይህ ድርጊት በሀገር አቀፍ ደረጃ ሲሰላ መንግስት ለነዳጅ ድጎማና ግዢ የሚያወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ለጥቂት ግለሰቦች ሲሳይ እያደረገው ይገኛል።
ይህንን ምዝበራ በዘላቂነት ለመፍታት በነዳጅ ጫኝ ተሽከርካሪዎች ላይ የቦታ እና የሁኔታ ጠቋሚ (Sensor) መሣሪያዎች ሊገጠሙ መሆኑን ገልፀው ይህም ከዴፖ የተጫነው የነዳጅ መጠን ማደያ ላይ እስከሚራገፍ ድረስ ያለውን ጉዞ በዲጂታል ካርታ ይከታተላል ብለዋል።
በነዳጅ ማጓጓዣ ሰንሰለት ውስጥ ያሉ በርካታ ተዋናዮችን ንክኪ በማስቀረት፣ አሠራሩን ሙሉ በሙሉ በቴክኖሎጂ የታገዘ አንደሚያደርግ ጠቁመው በመንገድ ላይ የነዳጅ ታንከሩ ያለፈቃድ ቢከፈት ወይም መጠኑ ቢቀንስ ወዲያውኑ ለቁጥጥር ማዕከሉ መረጃ ይልካል ሲሉ ገልፀዋል።
ይህ አዲስ አሠራር ቀደም ሲል ተግባራዊ ከተደረገው የዲጂታል ነዳጅ ግብይት (Telebirr) ጋር ተዳምሮ፣ በዘርፉ የሚታየውን ሰው ሰራሽ የነዳጅ እጥረትና የጥቁር ገበያ ንግድን በእጅጉ ይቀንሳል ተብሎ ይጠበቃልም ብለዋል።
ይህም ፍትሃዊ የነዳጅ ስርጭት እንዲኖርና የአገር ሀብት እንዳይባክን ትልቅ ሚና ይጫወታል ተብሎ ይገመታል።
ምስል በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ(AI) የበለፀገ
በአማኑኤል አክሎግ
#afromekina
Loading content...
