ቻይና የኤሌክትሪክ መኪና ስውር የበር እጀታዎችን አገደች
ቻይና ከመጪው የፈረንጆቹ ጥር 1 ቀን 2027 ጀምሮ ስውር የኤሌክትሪክ መኪና የበር እጀታዎች ላይ ሙሉ በሙሉ እገዳ መጣሏ ተዘገበ፡፡ በዚህም መሠረት ማንኛውም ተሽከርካሪ ከውስጥም ሆነ ከውጭ ሜካኒካል (በእጅ የሚሰሩ) መክፈቻዎች ሊኖሩት እንደሚገባ አዲሱ መመሪያ ያስገድዳል።
ይህ ውሳኔ በዋናነት ያነጣጠረው የአየር ፍሰትን ለመቀነስ ሲባል ለስላሳና ስውር የበር እጀታዎችን በሚጠቀሙ የኤሌክትሪክ መኪናዎች (EVs) ላይ ነው። ውሳኔው የመጣው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በደረሱ አሰቃቂ የመኪና አደጋዎች ወቅት፣ በተለይም በቅርቡ በደረሰ የዢያኦሚ (Xiaomi EV) የእሳት አደጋ ወቅት በሮች አልከፈት ብለው ለሰው ሕይወት ማለፍ ምክንያት መሆናቸውን ተከትሎ፣ ለተነሳው የደህንነት ስጋት ምላሽ ለመስጠት ነው።
አዲሱ ሕግ ምን ይላል?
• የጊዜ ገደብ፦ ቀድሞውኑ ፍቃድ ያገኙ የመኪና ሞዴሎች ለውጡን ተግባራዊ ለማድረግ የሁለት ዓመት የችሮታ ጊዜ ይሰጣቸዋል።
• የውስጥ መቆለፊያዎች፦ የመኪናው የውስጥ በር እጀታዎች በቋሚነት የሚታዩና ግልጽ ምልክት ያላቸው መሆን አለባቸው።
• ተጽዕኖው፦ እንደ Tesla እና BYD ያሉ ግዙፍ ኩባንያዎች ለቻይና ገበያ ሲሉ ዲዛይናቸውን ለመቀየር ይገደዳሉ። ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚያመርቷቸው ሞዴሎች ላይ ተፅዕኖ ሊኖረው ይችላል።
የዘርፉ ተንታኞች እንደሚሉት፣ ይህ እርምጃ ቻይና በኤሌክትሪክ መኪና ኢንዱስትሪ ያላትን የበላይነት በመጠቀም የዓለምን የደህንነት መስፈርት (Standard) ለመወሰን ያላትን ጉልበት ያሳየችበት ነው። ይህም በአውሮፓና በሌሎች ሀገራት የመኪና ዲዛይን ላይ ትልቅ ተጽዕኖ እንደሚኖረው ይጠበቃል።
#afromekina
