በነዳጅ ዋጋ ጭማሪው ሳቢያ የትራንስፖርት ታሪፍ መጨመር ያስቀጣል
የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ታህሳስ 1 ቀን 2018 ዓ.ም የተደረገውን የነዳጅ ዋጋ ማሻሻያን ተከትሎ ማንም አካል በገዛ ፍቃዱ የትራንስፖርት ዋጋ መጨመር እንደማይችል አስታወቀ። ጭማሪ የሚያደርጉ አሽሀርካሪዎች ላይ ከመስመር እስከማስወጣት የሚደርስ እርምጃ እንደሚወሰድ ቢሮው አስጠንቅቋል።
የቢሮው የኦፕሬሽን ዘርፍ ም/ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳኛቸው ሽፈራው ለመናኸሪያ ሬዲዮ በሰጡት ቃል፣ አንዳንድ አካባቢዎች ላይ በራስ ፈቃድ የዋጋ ማሻሻያ ሲደረግ እንደነበር ገልጸው፣ ቢሮው ከጠዋቱ 12 ሰዓት እስከ ምሽት 4 ሰዓት ድረስ ጥብቅ ቁጥጥር እያደረገ መሆኑን አብራርተዋል።
በምሽት የትራንስፖርት አገልግሎት ላይ ዋጋ የሚጨምሩ አሽከርካሪዎች ለየት ያለ ቅጣት የሚጠብቃቸው ሲሆን፣ እስከ አምስት ሺህ ብር በጭማሪው ብቻ እንደሚያስቀጣ ተጠቁሟል።
የነዳጅ ዋጋ ጭማሪውን ተከትሎ በታሪፍ ላይ የሚደረግ ማሻሻያ ካለ፣ ቢሮው ከትራንስፖርትና ሎጀስቲክ ጋር በመሆን ጥናት እያደረገ እንደሚገኝ አቶ ዳኛቸው ገልጸዋል።
ኅብረተሰቡም በመደበኛው ታሪፍ ብቻ በመክፈል መብቱን እንዲያስከብር ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፣ ጭማሪ ሲደረግ የተሽከርካሪውን የሰሌዳ ቁጥር፣ ሰዓትና ቦታ በመጥቀስ በቢሮው ነፃ የስልክ ጥሪ መስመር 9417 ጥቆማ እንዲያቀርብ ጠይቀዋል።
ቢሮው የሕዝብ ትራንስፖርት ሰጪ አካላት ያለምንም ታሪፍ ጭማሪ፣ በመደበኛው ታሪፍ መሰረት እስከ ምሽቱ 4 ሰዓት ድረስ አገልግሎት እንዲሰጡ ማሳሰቡን መናኸሪያ ሬዲዮ ዘግቧል፡፡
#afromekina
Loading content...
