ቱርክ በሶማሊያ የነዳጅ ቁፋሮ ልትጀምር ነው ተባለ
ቱርክ በአዲሱ የአውሮፓውያን ዓመት በሶማሊያ የባሕር ክልል ውስጥ ነዳጅ ለማውጣት ቁፋሮ እንደምትጀምር ፕሬዝዳንቷ ረሲፕ ታይብ ኤርዶዋን ተናገሩ።
ኤርዶዋን ይህንን የተናገሩት እስራኤል ለሶማሊላንድ የአገርነት ዕውቅና መስጠቷን ተከትሎ ድጋፍ ለማሰባሰብ ወደ ተለያዩ አገራት እያቀኑ ያሉት የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሼክ ሐሰን ሞሐመድ በተገኙበት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው።
ከአንድ ዓመት በፊት በሶማሊያና በቱርክ መካከል የተደረሰውን ዘርፈ ብዙ የትብብር ስምምነት ተከትሎ፣ ቱርክ ግዙፍ ነዳጅ አሳሽ መርከቦችን በሶማሊያ የባሕር ክልል ውስጥ አሰማርታ ፍለጋ ስታካሂድ ቆይታለች።
የቱርክ ፕሬዝዳንት ኢስታምቡል ውስጥ በተካሄደው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ላለፉት ዘጠኝ ወራት የተካሄደው የነዳጅ አሰሳ ተጠናቅቆ በአዲሱ የአውሮፓውያን ዓመት ነዳጅ ለማውጣት ቁፋሮ ይጀመራል።
በሕንድ ውቅያኖስ ላይ በሚገኘው የሶማሊያ የባሕር ጠረፍ ላይ ሰፊ ቦታን የቱርክ ነዳጅ ፈላጊ አሳሾች ፍለጋ ማካሄዳቸውን የጠቀሱት ኤርዶዋን፤ "ይህ ዓይነቱ ሥራ ለቱርክ አዲስ ነው" ሲሉም ተናግረዋል።
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ነዳጅ የማውጣት ቁፋሮው "በቅርቡ" ይጀመራል ሲሉ ኤርዶዋን ደግሞ "በአዲሱ ዓመት" እንደሚጀመር አመልክተዋል።
ለዚህም የቱርክ ተጨማሪ የነዳጅ መቆፈሪያ መርከቦችን ወደ አካባቢው እንደሚሰማሩ የቱርክ ፕሬዝዳንት መግለጻቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
#afromekina
Loading content...
