ኢትዮ ቴሌኮም 3ኛውን ፈጣን የኤሌክትሪክ መኪና ቻርጅ ማድረጊያ ጣቢያ ሥራ አስጀመረ
በሰው ሰራሽ አስተውሎት የተደገፈና የላቀ ቴክኖሎጂን የሚጠቀኢትዮ ቴሌኮም በአዲስ አበባ ከተማ ያስገነባውንና ሦስተኛውን ፈጣን የኤሌክትሪክ መኪና ቻርጅ ማድረጊያ ጣቢያ ሥራ አስጀምሯል።
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ በዚህ ወቅት÷ ጣቢያው በአንድ ጊዜ እስከ 16 ተሽከርካሪዎችን የማስተናገድ አቅም እንዳለውና ይህም ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችል ተናግረዋል።
በዛሬው ዕለት ስራውን የጀመረው የቻርጅ ማድረጊያ ጣቢያው፣ በሰው ሰራሽ አስተውሎት የተደገፈና እጅግ የላቀ ቴክኖሎጂን የሚጠቀም ሲሆን÷ ከተሽከርካሪዎቹ ዓይነት ጋር ራሱን የሚያጣጥም እጅግ ፈጣን ቻርጀር የተገጠመለት መሆኑም ተገልጿል።
ቀደም ሲል በኢትዮ ቴሌኮም የተገነቡ ሁለት ጣቢያዎችን ጨምሮ በአጠቃላይ በአንድ ጊዜ ለ48 የኤሌክትሪክ መኪኖች አገልግሎት መስጠት የሚያስችል አቅም መፈጠሩን ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ አብራርተዋል፡፡ አገልግሎት እየሰጡ በቆዩት የመጀመሪያዎቹ ሁለት የቻርጅ ጣቢያዎች ከ165 ሺህ በላይ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች አገልግሎት እያገኙ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
አሽከርካሪዎች አገልግሎቱን በራሳቸው ማግኘትና ክፍያቸውንም በቴሌብር ሱፐርአፕ መፈጸም እንደሚችሉ አንስተዋል።
ኩባንያው እያደገ የመጣውን የኢትዮጵያን የኤሌክትሪክ መኪና ስነ ምህዳር በስማርት ቴክኖሎጂ ለመደገፍ ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር ማሳየቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።
#afromekina
