"ነዳጅ ስለመሆኑ የሚያጠራጥር ነገር የለም "
" ነዳጁ በትክክል ወጥቶ መሬት ላይ እየታየ ነው ፣ በተሰነጠቁ መሬቶች አማካኝነት የወጣው ነዳጅ በአካባቢው የሚገኙ ውሃዎችን እየበከለ ነው " - የደቡብ ወሎ ዞን የማዕድን ሀብት ልማት መምሪያ
በደቡብ ወሎ ዞን ለገሂዳ ወረዳ የነዳጅ ክምችት በተፈጥሮ አስገዳጅነት ከከርሰ ምድር በላይ መውጣት ከጀመረ ከ7 አመታት በላይ ቢያስቆጥርም እስካሁን ጥቅም ላይ እንዲውል ባለመሰራቱ አሁንም የነዳጅ ድፍድፉ መሬቱን ሰንጥቆ እየወጣ መሆኑን የደቡብ ወሎ ዞን ማዕድን ሀብት ልማት መምሪያ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልጿል።
በመምሪያው የማዕድን ስራዎች እና ፍቃድ አስተዳደር ቡድን መሪ የሆኑት አቶ ጀማል እንዲሪስ ይህን የነዳጅ ክምችት አዋጪነቱ ተጠንቶ ጥቅም ላይ እንዲውል ለማድረግ በተደጋጋሚ ለማዕድን ሚኒስቴር ጥያቄ ሲያቀርቡ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
አቶ ጀማል እንዲሪስ በዝርዝር ምን አሉ ?
" ከዚህ በፊት በወረዳው ያለውን የነዳጅ ክምችት ጥቅም ላይ ለማዋል የተለያዩ ፕሮጀክቶች በግል ተቋማት እና በመንግስት ተቋማት ሲሞካከሩ ነበር። እኛም በየጊዜው ጉዳዩ የሚዲያ ሽፋን እንዲያገኝ ስናደርግ ቆይተናል።
እኛ ማድረግ የምንችለው ጥናት እንዲካሔድበት ግፊት ማድረግ ነው፣ በዚህም መሰረት በ 2011 ዓ.ም ማዕድን ሚኒስቴር በጉዳዩ ላይ ውይይት አካሒዶ ነበር። በሰአቱም ሀብቱ እንዳለ ከመሬት በላይ በምልክት ተጋልጦ እየታየ ስለሆነ ሀገራችን እና የአካባቢውን ማህበረሰብ እንዲጠቀም ለማድረግ ጥናት እንዲካሔድ ጥያቄ አቅርበንላቸው ተቀብለውን ነበር። ጥናት ለማካሔድም እቅድ መያዙን ነግረውናል፣ ከዛን በሗላ ግን ምንም አይነት እንቅስቃሴ እየተደረገ አይደለም።
እንደዞን አሁን ያለን ሃሳብ ጉዳዩ በተለያዩ ሚዲያዎች ሽፋን እንዲያገኝ ማድረግ እና ከላይ ያሉት የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት ሰጥተው ጥናት እንዲያደርጉ ጫና ማሳደር ነው። እኛ አቅደን የማንሰራው ጉዳይ ስለሆነ ፍላጎት እና ሀሳብ ነው ያለን። ምክንያቱም ይህን የመስራት ስልጣን የተሰጠው ማዕድን ሚኒስቴር ብቻ ነው።
ነዳጁ በትክክል ወጥቶ መሬት ላይ እየታየ ነው፣ በተሰነጠቁ መሬቶች አማካኝነት የወጣው ነዳጅ በአካባቢው የሚገኙ ውሃዎችን እየበከለ ነው። በዚህ የነዳጅ ክምችት ላይ ክልሉም፣ ዞናችንም፣ ወረዳውም ፍላጎታችን ተመሳሳይ ነው።
የለገሂዳ ወረዳ ኮሚኒኬሽን በተደጋጋሚ ትኩረት እንዲሰጠው እየጠየቀ ነው፣ አመራሮችም በየጊዜው በተገኙበት መድረክ ሁሉ ስለ ጉዳዩ ሳያነሱ አያልፉም፣ ነገር ግን የሚመለከተው አካል ' ጥናት እናደርጋለን ' ብሎ ቃል ከመግባት የዘለለ ነገር አያደርግም። አሁንም ጥያቄውን እያቀረብን ነው።
በመሆኑም አሁን ላይ በተሰነጠቀው መሬት ከላይ የሚፈሰውን ድፍድፉን የአካባቢው ማህበረሰብ በመውሰድ ለምሽት መብራትነት በኩራዝ በባህላዊ መንገድ እየተጠቀመበት ነው። ይህ ማዕድን ለሀገር ትልቅ ገቢ ቢሆንም ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ባለመሆኑ ነዳጁ እየባከነ ነው።
ከመሬት በላይ ያለው ወይም የሚታየው ድፍድፉ በጣም ቀጭን አይደለም፣ ግን በጣም ይሸታል፣ ተቀጣጣይ ነው፣ ለናሙና ቢሮ ያመጣነው አለ፣ ስናቀጣጥለው በጣም ይቀጣጠላል። ይህን የተፈጥሮ ሀብት ጥቅም ላይ ለማዋል መስራት የሚችለው እና በአዋጅ መብት የተሰጠው ማዕድን ሚኒስቴር ነው፣ በአቅም ደረጃም ቢታይ ወረዳው አይችልም።
ወሎ ዩኒቨርሲቲ ከዚህ በፊት የተለያዩ ባለሙያዎችን እና ተማሪዎቹን በስፍራው በመውሰድ ምልከታ አድርጎ ነዳጅ መሆኑን አረጋግጧል። በወቅቱ ባለሙያዎቹ አካባቢው በተዳከመ የመሬት Fault ነዳጁ ወደ ውጪ እንደወጣ ነው ያስረዱት። ነዳጅ ስለመሆኑ የሚያጠራጥር ነገር የለም " ሲሉ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።
#afromekina
Loading content...
