በቅርቡ በነዳጅ ምርቶች ላይ የሚጣለው ግብር ኢኮኖሚው ላይ ምን ለውጥ ሊያስከትል ይችላል ?
ከመጪው ታኅሣሥ ወር ጀምሮ በኢትዮጵያ የነዳጅ ምርቶች ላይ የ30 በመቶ ታክስ ይጣላል። ይህ የ30 በመቶ ታክስ፣ 15 ፐርሰንት የተጨማሪ እሴት እና 15 በመቶ ደግሞ የኤክሳይዝ ታክስ ድምር ነው።
የነዳጅ ምርት ላይ የ30 በመቶ ታክስ እንደሚጣል የተሰማው መንግስት ለነዳጅ ሲያደርገው የነበረው ደጐማ ሙሉ በሙሉ ከተነሳ በኋላ ነው።
አዲሱ የነዳጅ ግብር ከቀጣዩ ወር ጀምሮ በነዳጅ አቅራቢ ድርጅት አማካኝነት እየተሰበሰበ ለፌድራል መንግስት ገቢ ይሆናል።
ውሳኔው በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ምን ለውጥ ሊያስከትል ይችላል ?
በዮናይትድ ኪንግድም፣ ለንደን የሚገኙት የኢኮኖሚ ባለሙያው አብዱልመናን መሐመድ (ዶ/ር) የነዳጅ ምርቶች ላይ የሚጣለው ታክስ በተለይ በትራንስፖርቱ ዘርፍ ወዲያው የሚታይ ተፅህኖ ሊያሳርፍ እንደሚችል ለቲክቫህ ኢትዮጵያ አስረድተዋል።
“30% ታክስ ከፍተኛ ጭማሪ ስለሆነ በተለይ ትራንስፖርቱ ላይ ወዲያው ነው ተፅህኖ የሚታየው። የህዝብም፣ የሸቀጣሸቀጥም ትራንስፓርት ወዲያው ነው አፌክት የሚያደርገው። የአብዛኛውን ህይወት አይመለከትም እንጂ የአውሮፕላን በረራን እንዳለ አፌክት ያደርጋል። ያ ደሞ በካርጐ የሚመጡ እቃዎችንን እንዳለ ይነካል” ሲሉ ገልፀዋል።
የቢዝነስና ኢንቨስትመንት አማካሪው አቶ ከፈለኝ ኃይሉ በበኩላቸው ለቲክቫህ ሲገልፁ በቅርቡ ተግባራዊ የሚሆኑት የነዳጅ ግብሮች የዋጋ ግሽበት ሊያስከትል እንደሚችል ያነሳሉ።
“የነዳጅ ድጎማው ተነስቶ ነው ያለው። በዚህ ላይ ደግሞ አሁን ተጨማሪ [መንግስት] ለመሰብሰብ ያሰበው የተጨማሪ እሴት ታክስና ኤክሳይስ ታክስ አለ። ይኼ ማለት ወደ 30 በመቶ ነው። ከፍተኛ ነው። ቀጥተኛ ተጽህኖ አለው የሸማች ዋጋ ላይ ተፅህኖ ያመጣል ይኼ ግልፅ ነው።
የትራንስፓርት፣ የሎጀስቲክስ፣ የአግልግሎት፣ የግብዓት ዋጋ ይጨምራል። ዞሮ ዞሮ ሸቀጦች ላይ ዋጋ መጨመሩ አይቀረም። ይኼ ደሞ የዋጋ ግሽበት ላይ ጫናው እንዲጨምር ያደርጋል። በተለይ ደሞ ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ሰዎች ጫና መፈጠሩ ይጠበቃል” ሲሉ ይናገራሉ።
“ነዳጅ ማለት፣ ከሞላ ጐደል ሁሉነም ነገር የሚነካ ስለሆነነ የሚደረግ ጭማሪ የህብረተሰቡ ህይወት ላይ ውጤቱ ይንፀባረቃል” ሲሉ አብዱልመናን (ዶ/ር) ይነገራሉ።
ለመሆኑ የኢትዮጵያ መንግስት ይህንን ውሳኔ ለምን መወሰን አስፈለገው ?
ቲክቫህ ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ባለሙያው የሆኑት አብዱልመናን መሐመድ (ዶ/ር) መንግስት ይህንን ውሳኔ ለምን መወሰን አስፈለገው ? ስንል ጠይቋቸዋል።
“አሁን ታክስ እንደ አንድ የገቢ ምንጭ ነው። መንግስት የበጀት ዴፊሲት(የበጀት ጉድለት) አጋጥሞታል። ‘ራስህንቻል’ ተብሏል። እንደ ድሮ ብር ማተም የለም። እንደ ድሮ በቀላሉ ከውጪ ገንዘብ መበደር የለም። መንግስት ገቢው ላይ ነው ያተኮረው” የሚሉት አብዱልመናን (ዶ/ር) በዚህም ሳቢያ ከነዳጅ የሚገኘው ታክስ ለመንግስት አዲስ የገቢ ምንጭ እንሚሆን ጠቅሰዋል።
ታዲያ እነዚህ ሁለት የታክስ ዓይነቶች በቢሊዮን ብሮች ከሚያንቀሳቅሰው የነዳጅ ንግድ መንግስት ዳጎስ ያለ ገቢ እንዲያገኝ እንደሚረዳው አብራርተዋል።
በተጨማሪም ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት መንግስት ገቢውን እንዲያሳድግ እያደረጉ ያለው ጫና ሌላኛው ምክንያት ሊሆን ይችላል።
በሌላ በኩል ግን “የድጐማው” መቅረት እንዲሁም ተጨማሪ ገቢ መኖር መንግስት ወጪ እንዲቀንስ እና ገንዘብ ወደ ሌሎች አንገብጋቢ ዘርፎች እንዲያዞር ይረዳዋል ብለዋል።
በዚህ ሀሳብ የሚስማሙት የቢዝነስና ኢንቨስትመንት አማካሪው አቶ ከፈለኝ ደግሞ ይህ ታክስ መንግስት ገቢውን ከማሳደግ አልፎ ህገ ወጥ የነዳጅ ግብይትን በቀላሉ እንዲከላከል እንደሚረዳው ገልፀዋል።
ከጎረቤት ሀገራት አኳያ በኢትዮጵያ የነበረው ዝቅተኛ የነዳጅ ዋጋ ለህገወጥ የነዳጅ ንግድ ምክንያት እንደ ነበር አንስተዋል።
“አሁን ወደ ውጪ ወጥቶ ምንም ትርፍ ከሌለው ወይም የጐረቤቶቻችን ከቀነሰ [ነዳጅ ከኢትዮጵያ] የመውጣት ዕድሉን ይቀንሳል። ህገ ወጥ የሆነውን ድንበር ተሻግሪ የነዳጅ ንግድን ይቀንሰዋል” ካሉ በኃላ የነዳጅ ብክንነትንም ለማሰወገድ ይረዳል ሲሉ አክለዋል።
ሆኖም የኢኮኖሚ ባለሙያዎቹ ይህ አዲስ ታክስ አንስተኛ ንግዶችን፣ ኢንቨስትመንት እና የስራ ፈጠራን ሊጎዳ ይችላል የሚል ስጋት አላቸው።
የዘገባው ባለቤት #ቲክቫህ ኢትዮጵያ
#afromekina
Loading content...
