በአብዛኛዎቹ ተሽከርካሪዎች ላይ የሚገኙ የደኅንነት ቀበቶዎች ከደረጃ በታች መሆናቸው አደጋ የመከላከል አቅማቸው ላይ ጥያቄ እንደፈጠረ ተገለጸ
👉 የደህንነት ቀበቶ ያላሰሩ ከ23 ሺሕ በላይ አሽከርካሪዎችና ተሳፋሪዎች ክስ ተመስርቶባቸዋል ተብሏል
የሕዝብ ማመላለሻዎችን ጨምሮ በአብዛኛዎቹ ተሽከርካሪዎች ላይ የሚገኙ የደኅንነት ቀበቶዎች ከደረጃቸውን ያልጠበቁ መሆናቸው አደጋ የመከላከል አቅማቸው ላይ ጥያቄ መፍጠሩ ተገልጿል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የትራፊክ ቁጥጥር መምሪያ እና የኦሮሚያ ትራንስፖርት ባለስልጣን ተወካዮች ከአሐዱ ራድዮ ሁሉ ደህና ፕሮግራም ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት፤ የደኅንነት ቀበቶ ዋና ዓላማ በተሽከርካሪ ውስጥ ያለውን የተሳፋሪን ደኅንነት ማስጠበቅ ቢሆንም የአብዛኛዎቹ ተሽከርካሪዎች ቀበቶ ከደረጃ በታች በመሆኑ በአደጋ ወቅት የሚያጋጥመውን ጉዳት የመቀነስ ዕድሉን በእጅጉ ቀንሶታል፡፡
የኦሮሚያ ትራንስፖርት ባለሥልጣን የተሽከርካሪ ብቃት ቡድን መሪ አቶ ክብሩ ባይሳ የደህንነት ቀበቶን ለማሰር ፈቃደኛ ያለመሆን ጉዳይ በጥናት ሊፈተሽ እንደሚገባ አንስተዋል፡፡
"የደኅንነት ቀበቶ ማሰር ግዴታ ከሆነ በኋላ በቤት ተሽከርካሪዎች ላይ የሚደርሰውን አደጋ 45 ከመቶ ያህል ቀንሶታል"ያሉት ቡድን መሪው፤ አደጋ በደረሰበት ተሽከርካሪ ውስጥ የነበሩ ሰዎችን አካላዊ ጉዳት 60 በመቶ መቀነስ መቻሉን አብራርተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የትራፊክ ቁጥጥር መምሪያ የትራፊክ ሙያና የሕዝብ ግንዛቤ ዲቪዥን ኃላፊ ኢንስፔክተር ሰለሞን አዳነ በበኩላቸው፤ ከ23 ሺሕ 600 በላይ አሽከርካሪዎች በአዲስ አበባ ከተማ የደኅንነት ቀበቶ ሳያስሩ በማሽከርከራቸው ምክንያት ክስ እንደተመሰረተባቸው ተናግረዋል፡፡
ክሱ አሽከርካሪዎችን ብቻ ሳይሆን በተሽከርካሪ የፊት ወንበር /ጋቢና/ የተቀመጡ ተሳፋሪዎችንም ያጠቃልላል ብለዋል፡፡
የደኅንነት ቀበቶ አጠቃቀም ላይ እየተካሄደ የሚገኘው ቁጥጥር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ኢንስፔክተር ሰለሞን አስታውቀዋል፡፡
የተሽከርካሪዎች የደኅንነት ቀበቶዎችን በአግባቡ መጠቀም በአደጋ ወቅት የሚደርስን ጉዳት በከፍተኛ መጠን እንደሚቀነስ ቢገለጽም፤ በተለይ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ላይ የሚገኙት የደኅንነት ቀበቶዎች ከደረጃ በታች መሆናቸው አሳሳቢ ነው ተብሏል፡፡
#afromekina
Loading content...
