በ214 ሚ. ዶላር የሚገነባው ግዙፉ የትራንስፖርት ኮሪደር - በደቡብ ሱዳን-ኢትዮጵያ-ጅቡቲ
የአፍሪካ ልማት ባንክ በምሥራቅ አፍሪካ ያለውን የንግድና የትራንስፖርት ትስስር ይበልጥ ለማጠናከር የሚያግዝ የ214.47 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ለደቡብ ሱዳን-ኢትዮጵያ-ጅቡቲ የትራንስፖርት ኮሪደር (ምዕራፍ 2) ፕሮጀክት አጽድቋል። በዚህ የገንዘብ ድልድል መሠረት ኢትዮጵያ 181.5 ሚሊዮን ዶላር፣ ጅቡቲ 29.71 ሚሊዮን ዶላር፣ እንዲሁም ደቡብ ሱዳን 1.96 ሚሊዮን ዶላር የሚያገኙ ሲሆን፤ በተጨማሪም 1.30 ሚሊዮን ዶላር ከሽግግር ድጋፍ ተቋም (Transition Support Facility) ተመድቧል።
ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት በቀጠናው ያለውን የትራንስፖርት ፍሰት ለማቀላጠፍ በርካታ ሥራዎችን ያካተተ ሲሆን፤ በዋናነትም በኢትዮጵያ ውስጥ የ67 ኪሎ ሜትር የፍጥነት መንገድ (Expressway) ግንባታን ያካትታል። በተጨማሪም በጅቡቲ የሚገኘውን የ18 ኪሎ ሜትር የዲኪል-ሙሉድ መንገድን ወደ ላቀ ደረጃ የማሳደግና በኢትዮጵያና በጅቡቲ የሚገኙ አነስተኛ መጋቢ መንገዶችን የማሻሻል ሥራዎች ይከናወናሉ።
የፕሮጀክቱ ሌላኛው አካል በደቡብ ሱዳን በኩል የሚገኘውን የ280 ኪሎ ሜትር የካፖይታ-ቦማ-ራአድ መንገድን ግንባታ ለመጀመር የሚያስችሉ የጥናት ማሻሻያዎችን ማካተት ነው። ይህ የትራንስፖርት ኮሪደር ተጠናቆ ሲጠናቀቅ በሦስቱ ሀገራት መካከል ያለውን የሸቀጦች ልውውጥ ከማሳለጡም በላይ፣ ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን ከጅቡቲ ወደቦች ጋር ያላቸውን ትስስር በማጠናከር ለቀጠናው ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ትልቅ ሚና ይጫወታል።
#afromekina
Loading content...
