.የታክሲ ቁጥጥር ሥርዓቱ ሙሉ በሙሉ በቴክኖሎጂ ሊመራ ነው ተባለ
የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ እንዳስታወቀው፣ የታክሲ የቁጥጥር ሥርዓቱን ሙሉ በሙሉ በቴክኖሎጂ የሚመራ የሚያደርግ የዲጂታል ቁጥጥር አገልግሎት ሥራ ጀምሯል። ይህ አሰራር "ሞዴል ተርሚናል" በመፍጠር ረገድ ትልቅ እምርታ ሲሆን፣ በዘርፉ ለዓመታት የቆዩትን ብልሹ አሰራሮችና ሕገወጥ እንቅስቃሴዎች ወደ "ዜሮ" ለማውረድ የታለመ ነው።
የክፍለ ከተማው የትራንስፖርት ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሱራፌል ባያብል እንደገለጹት፣ አዲሱ ቴክኖሎጂ ቀደም ሲል በቄራ ተርሚናል በሲሲቲቪ ይደረግ የነበረውን ክትትል ወደ ላቀና ይበልጥ ግልጽነት ወዳለው ደረጃ ያሳደገ ነው። ይህ "ዲጂታል አይን" የታክሲ ተራን፣ የታሪፍ አተገባበርንና ሕገወጥ ጭነቶችን በንቃት በመቆጣጠር የታክሲ ባለንብረቶችንም ሆነ ተሳፋሪዎችን ሲያማርር የነበረውን የመረጃ መዛባትና የአሰራር መጓተት በዘላቂነት ይፈታል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳኛቸው ሽፈራው በበኩላቸው፣ ይህ የቴክኖሎጂ ሞዴል የትራንስፖርት አገልግሎትን የማዘመን ስትራቴጂ አንድ አካል መሆኑን አብራርተዋል። በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የተጀመረው ይህ ዘመናዊ አሰራር፣ ለሌሎች የከተማዋ ተርሚናሎች እንደ አርአያ በመሆን መላዋ አዲስ አበባ ወደ ዘመናዊ የዲጂታል ቁጥጥር ሥርዓት እንድትገባ መንገድ ጠራጊ ይሆናል።
በአማኑኤል አክሎግ
#afromekina
