የነዳጅ ክፍያ ተሰብሳቢ ዕዳ ከ200 ቢሊዮን ብር በላይ ደረሰ
ከኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ ተመን ማሻሻያ በኋላ የነዳጅ ክፍያ ተሰብሳቢ ዕዳ በከፍተኛ ሁኔታ በማደግ ከ200 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱን የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታውቋል።
የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ዶክተር ካሳሁን ጎፌ የዘርፉን ችግሮች ለመፍታት በተዘጋጀ ኮንፍረንስ ላይ እንደገለጹት፣ ከማሻሻያው በፊት 59 ቢሊዮን ብር የነበረው ተሰብሳቢ ዕዳ አሁን ላይ ከሦስት እጥፍ በላይ ጭማሪ አሳይቷል።
መንግሥት ለነዳጅ ግዢ በዓመት እስከ 700 ቢሊዮን ብር የሚመድብ ቢሆንም፣ ይህ እያደገ የመጣው ዕዳ ለሀገሪቱ የልማት ትልም ትልቅ ተግዳሮት እየሆነ መምጣቱን ሚኒስትሩ አብራርተዋል።
ይህንን ፈታኝ ሁኔታ ለመቀልበስ መንግሥት ቀደም ሲል ይከተለው የነበረውን በብድር ለኩባንያዎች ነዳጅ የማከፋፈል አሠራር በማስቀረት፣ ኩባንያዎቹ ለነዳጁ ቅድመ ክፍያ እንዲፈጽሙ የሚያስገድድ አዲስ መመሪያ ተግባራዊ አድርጓል።
አዋጅ ቁጥር 1363/2017ን መሠረት ያደረገው ይህ እርምጃ የሀገርን ጥቅም ለማስጠበቅ የተወሰደ ቢሆንም፣ በዘርፉ ላይ የሚስተዋሉ መዋቅራዊ ችግሮችን እስካላስወገድን ድረስ ውጤታማ ነን ማለት አንችልም ሲሉ ዶክተር ካሳሁን በቅንጅት የመሥራትን አስፈላጊነት አጽንኦት ሰጥተዋል።
ነዳጅ ለሀገር ደኅንነትና ለኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ወሳኝ ስትራቴጂክ ምርት በመሆኑ፣ ወቅታዊ ተግዳሮቶችን በአዋጅና በመመሪያው መሠረት መፍታት እንደሚገባም ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።
በሌላ በኩል የነዳጅ አቅራቢ ኩባንያዎችና የንግድ ማኅበራት አዲሱ የቅድመ ክፍያ አሠራር በሥራ ካፒታላቸው ላይ ጫና እየፈጠረ መሆኑን በመግለጽ ቅሬታቸውን እያሰሙ ይገኛሉ።
ሚኒስቴሩ ግን ተዓማኒነትን የሚሸረሽሩና የሀገሪቱን ዕድገት የሚያደናቅፉ አሠራሮችን ለማረም የግዴታ እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚቀጥል አስታውቋል። ይህ ከፍተኛ ዕዳ በሀገሪቱ የፋይናንስ ሥርዓትና በዋጋ ግሽበት ላይ ተጨማሪ ጫና እንዳይፈጥር ሥጋት የፈጠረ ሲሆን፣ መንግሥት ከባንኮችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ዕዳውን የመሰብሰብ ሥራን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተመላክቷል።
#afromekina
Loading content...
