የቦሌ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ከምሽቱ 2 እስከ ሌሊቱ 9 ሰዓት የጠጥቶ ማሽከርከር ቁጥጥር አካሄደ
• 38 አሽከርካሪዎች ከልኬት በላይ ጠጥተው በማሽከርከራቸው ተቀጥተዋል
*
በአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን የቦሌ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በጥር ወር በተያዘው የመንገድ ደህንነት ግንዛቤ ማስጨበጫና ቁጥጥር ንቅናቄ መርሃ ግብር ከክ/ከተማው ማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስና ከትራፊክ ፖሊስ አባላት ጋር በመሆን በትናንትናው እለት የተቀናጀ ኦፕሬሽን አካሂዷል፡፡
ባካሄደው የተቀናጀ የጠጥቶ ማሽከርከር ቁጥጥር ሂደትም 780 አሽከርካሪዎች ላይ የትንፋሽ ቁጥጥር በማድረግ 38ቱ ከልኬት በላይ ጠጥተው ሲያሽከረክሩ በመገኘታቸው በገንዘብ ሲቀጡ 63ቱ ከልኬት በታች በመሆኑ ትምህርት ተሰጥቷቸው እንደታለፉ ጽ/ቤቱ በላከው መረጃ አስታውቋል፡፡
የጽህፈት ቤቱ መረጃ እንዳመለከተው ፍተሻው የተካሄደባቸው መስመሮች ገርጂ መብራት ሃይል ዝኪር ባርና ሬስቶራንት አካባቢ መሆኑን ጠቅሶ ጠጥቶ በማሽከርከር አደጋ የሚደርሰው ለሊት ላይ መሆኑን በመገንዘብ የተጠናከረ ኦፕሬሽን በተጠቀሱት ሰዓታት መካሄዱን አመላክቷል፡፡
የቀዳሚ አደጋ መንስኤ የሆነውን የጠጥቶ ማሽከርከር ሁኔታን ለመከላከል ስልታዊ አቅጣጫ በመቀየስ ተግባሩን ማከናወኑን ያስታወቀው ጽ/ቤቱ ይኸው አሰራር በቀጣይ ሳምንታትም በሌሎች አካባቢዎች አጠናክሮ እንደሚያስቀጥል ጠቁሟል፡፡
በደንብ 557/2016 በልዩ ደረጃ ጥፋት ስር ከ 0.24- 1.0 ሚሊ ግራም በሊትር የአልኮል መጠን በትንፋሽ ውስጥ የተገኘበት አሽከርካሪ ከ 1,500 እስከ 3,000 ብር በገንዘብ እንደሚቀጣና በጥፋቱም ከ3 ነጥብ እስከ 8 ነጥብ እንደሚመዘገብብት ተቀምጧል፡፡
#afromekina
Loading content...
