በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የሆነው የነዳጅ ምርት መፈተሻ ላብራቶሪ በድሬደዋ ስራ ሊጀምር ነው
ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት (WTO) አባል ለመሆን በመጨረሻው ምዕራፍ ላይ በመገኘቷ እና የአህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጠና ተሳታፊ በመሆኗ፣ ከመቼውም ጊዜ በላይ ጥራት ያላቸውን ምርቶች ለገበያ ማቅረብ እንዳለባት ተገለጸ።
ምርቶች በአህጉራዊና ዓለም አቀፍ ገበያ ሲቀረቡ የዓለም አቀፍ ተቋማትን መስፈርት ማሟላት እንደሚጠበቅባቸው የገለጹት የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር መዓዛ አበራ ናቸው። ምርቶች ወደ ውጭ ሲላኩም ሆነ ወደ አገር ውስጥ ሲገቡ ከደረጃ በታች እንዳይሆኑ ከሚያስፈልጉ መሠረተ ልማቶች መካከል የጥራት መቆጣጠሪያ ተቋማት ዋነኞቹ መሆናቸውን ኢንጂነር መዓዛ አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት ከዋናው መሥሪያ ቤት በተጨማሪ እንደ አዳማ፣ ሀዋሳ እና ጅማ ባሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በሚገኙባቸው አካባቢዎች የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት የጥራት ፍተሻ ማዕከላትን እያስፋፋ ይገኛል።
በቀጣይ ሳምንታትም በድሬደዋ ከተማ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነው የነዳጅ ምርት ጥራት መፈተሻ ላብራቶሪ ሥራ እንደሚጀምር ኢንጂነር መዓዛ ለመናኸሪያ ሬዲዮ ተናግረዋል።
ድሬደዋ የነጻ ንግድ ቀጠና እንደመሆኗ፣ ከአህጉሩ የሚገቡም ሆነ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች ጥራታቸው በቀላሉ ተረጋግጦ እንዲዘዋወሩ ያስችላል ሲሉ ኢንጂነር መዓዛ ገልጸዋል።
የላብራቶሪ ማዕከላትን መገንባትና ተደራሽ ማድረግ የድርጅቱ ተቀዳሚ ተግባር መሆኑን አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት ባለፈው ቅዳሜ በአዳማ ከተማ ያስገነባውን የፍተሻ ላብራቶሪ ቅርንጫፍ ማዕከል፣ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ዶክተር ካሳሁን ጎፌ በተገኙበት በይፋ ማስመረቁ ይታወሳል።
#afromekina
Loading content...
