አናሃማ ትሬዲንግ አዳዲስ የኤሌክትሪክ የጭነት መኪኖችን ለገበያ አቀረበ
አናሃማ ትሬዲንግ ከአለም አቀፉ የኮንስትራክሽን መሣሪያዎች አምራች XCMG ጋር በመተባበር፣ ከአምስት እስከ ሃያ ቶን የመጫን አቅም ያላቸውን የኤሌክትሪክ የጭነት መኪኖች በዛሬው ዕለት በሚሊኒየም አዳራሽ ባከናወነው መርሃ ግብር አስተዋውቋል።
እነዚህ የደረቅ ጭነትና የቫን መኪኖች በከፊል በሀገር ውስጥ የሚገጣጠሙ ሲሆን፣ መንግስት የጀመረውን የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ ለመደገፍ ታስበው የቀረቡ ናቸው ተብሏል።
በማስተዋወቂያ መርሃ ግብሩ ላይ እንደተገለጸው፣ መኪኖቹ የአካባቢ ብክለትን ከመቀነሳቸው ባለፈ የአምስት ዓመት የባትሪ ዋስትና እንደተሰጣቸው ተገልጿል።
በተጨማሪም ገዢዎች ግዢውን እንዲያከናውኑ ለማገዝ እስከ 70 በመቶ የሚደርስ የባንክ ብድር መመቻቸቱ ተጠቅሷል።
ኩባንያው በኢትዮጵያና በጅቡቲ የXCMG ብቸኛ ወኪል በመሆኑ፣ በቀጣይ የኤሌክትሪክ መኪኖችን ተደራሽነት ለማስፋት እንደሚሰራ አመልክቷል።
አናሃማ ትሬዲንግ ባለፉት 30 ዓመታት በሀገር ውስጥ የማሽነሪ ኢምፖርት፣ ኤክስፖርትና ኪራይ ዘርፍ የተሰማራ ሲሆን፣ በተለይም እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ፣ የኮሪደር ልማትና የመንገድ ግንባታ ባሉ ትላልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ላይ ሲሳተፍ መቆየቱ ተነስቷል።
ኩባንያው በታማኝ ግብር ከፋይነቱም ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት እውቅና ማግኘቱን አስታውሷል።
ከንግድ ስራው ጎን ለጎንም በአዲስ አበባ ከተማ በቀን 6,000 አቅመ ደካሞችን በመመገብ ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝ በመርሃ ግብሩ ላይ ተነግሯል።
ድርጅቱ ከማሽነሪ አቅርቦት ባለፈ ወደ ማዕድን ማውጣት፣ ወደ አምስት ኮከብ ሆቴል ግንባታና ወደ ምግብ ማቀነባበሪያ ዘርፎች ለመግባት ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ገልጿል።
#afromekina
Loading content...
