ተገልጋዮች የትራንስፖርት አገልግሎት በመጠበቅ ከ12 ደቂቃ በላይ እንዳይቆሙ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ
👉 ሠራተኞችን ለመቆጣጠር የተገጠሙ የጂፒኤስ እና ካሜራ ዘዴዎች ውጤት አምጥተዋል ቢባልም የማይሰሩ እንዳሉም ተጠቁሟል
ተገልጋዮች የትራንስፖርት አገልግሎት በመጠበቅ ከ12 ደቂቃ በላይ እንዳይቆሙ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አውቶብስ አገልግሎት ድርጅት ለአሐዱ ሬዲዮ አስታውቋል፡፡
ይህን ለማድረግ የታሰበውም በደህንነት ካሜራ የታገዘ የመጓጓዣ ስርዓትን ወይም “ኢንተለጀንስ ትራንስፖርት ሲስተምን” በመጠቀምና ዘመናዊ አሰራሮችን በመዘርጋት ነው ሲሉ፤ የአገልግሎት ድርጅቱ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ እና የኦፕሬሽን እና የኢንተለጀንት ትራንስፖርት ሲስተም ኃላፊ አቶ ደገፋ ገብረመድህን ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘም ድርጅቱ የአውቶብሶችን እንቅስቃሴ እና አንድ ቦታ ላይ ቆመው የሚያሳልፉትን የጊዜ መጠን እንዲሁም፤ ሠራተኞች የሚያሳዩትን ያልተገባ ሥነ ምግባር ለመቆጣጠር ካሜራዎችን እና የጂፒኤስ አሰራሮችን መግጠሙን አስታውቋል፡፡
ሆኖም ሠራተኞችን ለመቆጣጠር የተገጠሙ የጂፒኤስ እና ካሜራ ዘዴዎች ውጤት አምጥተዋል ቢባልም፤ የማይሰሩ የጂፒኤስ መቆጣጠሪያ እና ካሜራዎች መኖራቸው ነው የተገለጸው፡፡
'ከተገጠሙት ካሜራዎች ውስጥ የማይሰሩ እንዳሉ' አሐዱ መታዘቡን ገልጾ ላቀረበላቸው ጥያቄ ኃላፊው በሰጡት ምላሽ፤ የተገጠሙት ካሜራዎች ከሲስተም ጋር የተያያዙ እና በየጊዜው ማዘመን የሚፈልጉ በመሆናቸው ምክንያት በተቋሙ በኩል ዘርፍ ተቋቁሞ ሥራዎችን እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተቋሙ እይታ 95 ከመቶ የሚሆኑት ካሜራዎች እንደሚሰሩ መረጋገጡን የገለጹም ሲሆን፤ የኢንተለጀንስ ትራንስፖርት ስርዓትን በማስፋት ችግሮችን ለመፍታት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
የአገልግሎት መስሪያ ቤቱ ከዚህ በፊት በተለያዩ የመቆጣጠሪያ ዘዴዎች በመጠቀም 105 የሚሆኑ ሠራተኞች ላይ የተለያዩ እርምጃዎችን መውሰዱን መግለጹ የሚታወስ ነው፡፡
#afromekina
Loading content...
