11 የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ኃይል መሙያ ጣቢያዎች ተመረቁ
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በአዲስ አበባና በተለያዩ የክልል ከተሞች ያስገነባቸውን በ6 ከተሞች የተገነቡ 11 የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ኃይል መሙያ ጣቢያዎች መመርቁን አስታውቋል።
አዲሶቹ ጣቢያዎች በአዲስ አበባ፣ ቢሾፍቱ፣ ሞጆ፣ ባቱ፣ አዳማ እና ሐዋሳ ከተሞች የተገነቡ ሲሆን፣ በአንድ ጊዜ ለ96 ተሽከርካሪዎች ፈጣን አገልግሎት የመስጠት አቅም አላቸው ብለዋል።
ተቋሙ ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ ካስገነባቸው 3 ጣቢያዎች ጋር ተደማምሮ፣ በአሁኑ ወቅት 14 ጣቢያዎችን ለአገልግሎት ማብቃት ተችሏል ሲሉ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ጌቱ ገረመው ለብስራት ሬዲዮ ተናግረዋል።
ይህም በቀን 24 ሰዓት ሙሉ እስከ 150 ተሽከርካሪዎችን በአንድ ጊዜ ማስተናገድ የሚያስችል አቅም ፈጥሯል።
ጣቢያዎቹ 24 ሰዓት ያለማቋረጥ አገልግሎት የሚሰጡ ሲሆን የቻርጅ ክፍያውም በሚጠቀሙበት ሰዓት መሠረት የተለያየ ተመን ተዘጋጅቶለታል።
በዚህም ከምሽቱ 4 ሰዓት እስከ ጠዋቱ 12 ሰዓት ለአንድ ኪሎዋት 14 ብር ከ85 ሳንቲም፣ ከጠዋቱ 4 ሰዓት እስከ ቀኑ 11 ሰዓት 16 ብር ከ57 ሳንቲም፣ ከቀኑ 11 ሰዓት እስከ ምሽቱ 4 ሰዓት እንዲሁም ከጠዋቱ 12 ሰዓት እስከ ረፋዱ 4 ሰዓት 18 ብር ከ28 ሳንቲም ክፍያ እንደሚፈጸም አገልግሎቱ ገልጿል።
የክፍያ ልዩነቱ የኤሌክትሪክ ፍላጎት በሚቀንስባቸው ሰዓታት ተጠቃሚዎች በዝቅተኛ ዋጋ መኪኖቻቸውን እንዲሞሉና ወጪያቸውን እንዲቆጥቡ ለማበረታታት መሆኑንም አመልክቷል።
በቀጣይም የቻርጅ ጣቢያዎችን ወደ ሌሎች ከተሞች ለማስፋፋት እቅድ ሲሉ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ጌቱ ገረመው ለጣቢያችን ገልጸዋል።
#afromekina
Loading content...
